የኤልጂቢቲኪው ሰዎችን በተለይም ከሁለትዮሽ ስርዓተ-ፆታ ማንነት ውጪ የሆኑ ሰዎችና ሴቶችንና በሥራዋ ማዕከል የምታደርገው፣ ኩዊር ትልቅ የሰውነት ቅርጽ ያላት ናይጄሪያዊቷ ፎቶግራፍ ባለሙያ አሌክዛንድራ ኦቦቺ።
አስደናቂ ምስሎቿ እንደ ቮግ ባሉ ፋሽን መፅሔቶች ላይ ታይተዋል፤ ነገር ግን አሌክዛንድራ ኦቦቺ ኤልጂቢቲኪው+ ናይጄሪያውያንን በፎቶዋ በግልጽ ማሳየት፣ በሥነ-ጥበብ አማካኝነት 'የወንድ የበላይነት ስርዓትን ለመጋፈጥ' የሚደርገው በጣም ሰፊ ጥረት አካል ነው ትላላች።
በዳንኤል አንተኒ
በናይጄሪያ ውስጥ ኩዊር ሰው ሆኖ በግልፅ መኖር ማለት፣ ታይነትህ በዓለም ውስጥ የምትጓዝበትን መንገድ እንዴት እንደሚቀይር በፍጥነት እንድትረዳ ያደርግሃል። ማንነታቸውን በሥነ-ጥበባቸው የሚገልጹ የፈጠራ ባለሙያዎች ደግሞ፣ ፍርሃት ሕይወታቸውን እንዳይመራ ሳይፈቅዱ፣ በጠላትነት በተሞላ አካባቢ በጥንቃቄ መጓዝ ማለት ነው። የፎቶግራፍ ባለሙያዋ አሌክዛንድራ ኦቦቺ በዚህ ቀችን መስመር ላይ መጓዝ ምን እንደሚሰማ በሚገባ ታውቃለች።
ኦቦቺ፤ ገና በ27 ዓመቷ በሚያስደምሙ ምስሎችዋ ከፍተኛ ትኩረትን መሳብ ችላልች። እንደ ቮግ እና ዴዝድ ባሉ ዓለም አቀፍ መፅሔቶች ላይ እንዲሁም እንደ ዘ ኔቲቭበመሳሰሉት የሀገር ውስጥ እትሞች ላይ በመቅረብ፤ ፎቶዎቿ ኤልጂቢቲኪው ሰዎችን ጨምሮ፣በናይጄሪያ ህብረተሰብ ወደ ዳር የተገፉ አካላትንና ማንነቶችን አጉልተው ያሳያሉ። ርህራሄ እና በራስ መተማመን በአብዛኛዎቹ ስራዎቿ ውስጥ ይንፀባረቃል፤ ይህም ኩዊርነትን በጥልቀት፣ በቅርበትና በረቂቅነት የሚመረምሩ ሥራዎችን ይፈጥራል።
ኦቦቺ፤ በመጽሔት ገፆች ሆነ በራሷ መድረኮች ላይ በምታጋራቸው ሥራዎች፣ እንደ ኩዊር ሴት ያላትን ማንነት ፈጽሞ አትደብቅም።ከዚህም በላይ፣ ይህንን ማንነቷን በብዙ ሥራዎቿ ውስጥ በግልጽ አስቀድማ አቅርባዋለች። በአቡጃ የምትኖረው እና የምትሰራው፣ ፎቶግራር ማንሳትን ሙያን በራሷ ጥረት፣ ራሷን ያስተማረችው ኦቦቺ፣ "እኔ ኩዊር ስለሆንኩ፣ በሄትሮኖራማቲቭ (በተቃራኒ ፆታ ግንኙነትን ብቸኛው መንገድ ነው ብሎ በሚያስብ አመለካከት) እና በፓትርያርኪ (የወንድ የበላይነት ስራዓት) አስተሳሰብ አልታሰርኩም" ትላልች። "ይህ ዓለምን እና ስራዬን ከተለያዩ እይታዎች እንድቃኝ አስችሎኛል። ኩዊርነቴ ማድረግ የምችለውን አይገድበኝም፤ እኔ ወደምመርጠው ማንኛውም አቅጣጫ ማደግና መስፋፋት እችላለሁ።”
ኦቦቺ ስለ ፈጠራ ስራ ስታወራ ልዩ ህያውና የሚስብ ድባብ ይታይባታል። በውይይት መካከል እንኳን ሃሳቦቿ፣ ከሚገልጿቸው ቃላት የበለጠ ፍጥነት ያላቸው ይመስላሉ። ብዙ ጊዜ ፈገግ ትላለች፣ ቀደም ብላ ወደ ጠቀሰቻቸው ሐሳቦች ተመልሳ ትገባለች፤ ስለ የምስል ሥነ-ጥበብ ስታወራም እንደ ሙያ ብቻ ሳይሆን፣ ከማንነቷ ጋር ፈጽሞ የማይነጣጠል የሕይወቷ አካል እንደሆነ ትናገራለች።
"ሁልጊዜ ባይሳካም፣ ተመልሼ ደግሜ ከመሞከር አልቦዝንም፤" ስትል ፈገግ እያለች፤ በፋሽን፣ ሜካፕ እና ስታይል ዙሪያ የምትፈጥራቸውን የፎቶ እና ሁለገብ ፈጠራ ስራዎች እና ዝግጅቶችን እየጠቀሰች ትናገራለች። "ትንሽ እብድ እንደሆንኩ የማውቀው በዚህ መንገድ ነው።"

የአሌክዛንድራ ኦቦቺ ፎቶግራፎች የግል ቅርበትን፣ ማንነትን፣ ትስስርና የባለቤትነት ስሜትን ይመረምራሉ፤ በተለይም ርኅራሄን በዕለት ተዕለት ሕይወት እንዴት እንደሚገለጥ በጥልቅ ፍላጎት ትመለከታለች።
በድፍረት መኖር
ኦቦቺ በናይጄሪያ የፈጠራ ዘርፎች ውስጥ ከሚሠሩና የኤልጂቢቲኪው+ ማንነታቸውን በግልፅ ከሚኖሩ ጥቂት፣ ነገር ግን ታይነታቸው እየጨመረ ከመጣ ናይጄሪያውያን መካከል አንዷ ናት። ሥራቸውን ለሚያደንቁ ሰዎች፣ የሥራዎቻቸው መስህብ በይዘታቸው ብቻ ሳይሆን፣ የሚወክሉት የተስፋና ምን መሆን እንድሚቻል ማሳያም ነው።
የኦቦቺ የፎቶግራፍ ሥራዎቿ አድናቂና ጓደኛ የሆነው ቦላጂ፣ በናይጄሪያ ውስጥ ይፋ ወጥቶ ወይም የኤልጂቢቲኪው ማንነትን ግልፅ አድረጎ መኖር የሚያስከትለው ጫና ቢኖረም፣ ህይወትን በሚያስደንቅ ግልፅነት የምትኖር ሰው እንደሆነች ይገልፃታል። “አሌክዛንድራን ስመለከት በድፍረት የሚኖር ሰው አያለሁ” ብሏል።
የኦቦቺ ታይነት ከኤልጂቢቲኪው እና ትልቅ የሰውነት ቅርጽ (ፕላስ ሳይዝ) ማህበረሰቦች ባሻገርም ትርጉም አለው። ቦላጂ በማንነታቸው ምክንያት መገለል ለሚገጥማቸው ለሌሎች “የተስፋ መገለጫ” በማለት ይገልፃታል።
ቀልብን ከሚስቡ ምስሎቿና ከራሷ ልዩ እይታ በተጨማሪ፣ ኦቦቺን ለየት የሚያደርጋት፣ ለኤልጂቢቲኪው+ ሰዎች አሁንም ጥልቅ ጥላቻ ባለባት አገር ውስጥ ስለ ማንነቷ ምንም ዓይነት እፍረት በውስጧ እንዲሰርጽ አለመፍቀዷ ነው።
“ኩዊር በመሆኔ ራሴን ጠልቼው ወይም ተጸይፌው አላውቅም። ሰዎች ከማንነትና ራስን ከመግለጽ ጋር በተያያዘ በጣም ፈራጅና ጭፍን ጥላቻ የተሞላባቸው ቢሆኑም፣ ያንን የማንነቴን ክፍል ተቀብዬ መኖርን ተምሬያለሁ፣” ትላለች ኦቦቺ። “ማህበረሰቡ በባህልና ወግ በጣም የተገደበ በመሆኑ፣ ሰዎች ከለመዷቸው ወጎችና ልማዶች ጋር የማይጣጣም ማንኛውም ነገር ተቃውሞ ይገጥመዋል።”
ነገር ግን በናይጄሪያ የወሲባዊና የስራዓተ-ፆታ ማንነት አናሳ ቡድኖች የሚገጥማቸው ተቃውሞ፣ በዕለት ተዕለት ኑሮ ከሚያጋጥማቸው መገለልና የደኅንነት ስጋቶች ያለፈ ሊሆን ይችላል። ከባድ ሕጋዊ መዘዞችንም ሊያስከትል ይችላል።

በአሌክዛንድራ ኦቦቺ “ሰለብሬቲንግ ኩዊርስ” ፕሮጀክት ውስጥ ከተካተቱ ሰዎች አንዳቸው። በናይጄሪያ፣ የኤልጂቢቲኪው ሰዎች ወንጀለኛ ተደርገው ከመቆጠራቸው ባሻገር፣ ድምፃቸው ይታፈናል፣ ይገለላሉ፣ ከማህበረሰቡም ይሰረዛሉ።
በናይጄሪያ ፌዴራል ሕግ መሠረት፣ በሁለት ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው አዋቂ ሰዎች መካከል በፈቃደኝነት የሚፈጸም የወሲብ ግንኙነት፣ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን እስከ 14 ዓመት በእስር ሊያስቀጣ ይችላል። ሃይማኖታዊውን የሸሪዓ ሕግ በሚተገብሩ አንዳንድ የሰሜን ግዛቶች፣ ቅጣቱ ከፆታ ልማዳዊ ደንቦች ውጭ በሆኑ ድርጊቶች ምክንያት ከሚጣል የግርፋት ቅጣት አንስቶ፣ ለአንዳንድ የተመሳሳይ ፆታ ወሲባዊ ድርጊቶች እስከ ሞት ቅጣት ሊደርስ ይችላል። እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ክልከላ ሕግ (ሴም ሴክስ ማሬጅ ፕሮሂቢሽን አክት) በአገሪቱ የኤልጂቢቲኪው+ ሰዎች መደራጀት፣ ታይነትና ራስን በይፋ መግለጽ ላይ ያሉትን ገደቦች የበለጠ አጥብቋል።
የኤልጂቢቲኪው ሰዎች ወንጀለኛ ተደርገው በሚቆጠሩባቸው አገራት ብዙውን ጊዜ፣ በቤተሰብና በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ማንነትን ግልጽ አድርጎ መኖር ቀጣይነት ያለው ጥንቃቄና ሚዛን የጠበቀ እርምጃ ግድ ይላል። ኦቦቺ ይህንን በራሷ ሕይወት አጋጥሟታል። ያለፈቃዷ ማንነቷ ለወላጆቿ ይፋ ከተደረገ በኋላ የተፈጠረው ውጥረት እስኪረጋጋ ድረስ ለአጭር ጊዜ ከቤት ለቃ ለመውጣት ተገዳ ነበር።
“ማንነቴ ያለፈቃዴ ለቤተሰቤ ይፋ መውጣቱ፣ በጣም አስከፊ ገጠመኝ ነበር፤ ድንበሬ እንደተጣሰም እንዲሰማኝ አድርጎኛል” ስትል በርጋታ ድምፅ ትገልፃለች። “ይህ በተፈጠረበት ወቅት ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ላይ ነበርኩ፤ ወሲባዊ ዝንባሌዬን ለመረዳትና ለመቀበል እየሞከርኩ ነበር። ማንነቴ ያለፈቃዴ ይፋ መሆኑ ያንን ሂደት ሙሉ በሙሉ አወከው፤ በመጨረሻም ከቤት ወጥቼ ከአንድ ሳምንት በላይ ቆየሁ።”
ኦቦቺ እንደምትለው፣ ወደ ቤት ከተመለሰች በኋላ ወላጆቿ ቀስ በቀስ የወሲባዊ ዝንባሌዋን ተቀብለዋል፤ ይሁን እንጂ ስለ ማንነቷ በግልጽ እንዳትናገርና ድብቅ እንድታደርገው ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ነበር። ከቤተሰቧ ጋር ያላትን ግንኙነት ፍቅርና ድጋፍ የተሞላበት ብላ ብትገልጸውም፣ ያገኘችው ተቀባይነት የራሱ ወሰን እንዳለውም ትረዳለች።
በናይጄሪያ የፈጠራ ባለሙያዎች ማህበረሰብ ውስጥ እንኳን፣ አንዳንዶቹ ከሰፊው ህበረተሰብ ይልቅ ለኤልጂቢቲኪው+ ሰዎች የበለጠ ተቀባይነት እንዳላቸው ቢታሰብም፣ ታይነትን በተመለከተ በፅሑፍ ያልሰፈሩ ማህበራዊ ደንቦች፣ ሰዎች ማንነታቸውን ምን ያህል በግልጽ የሚኖሩበትንና የሚገልጹበት መንገድ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን ቀጥለዋል።

የአሌክሳንድራ ኦቦቺ የፈጠራ ጉዞ በሜካፕ ሥነ-ጥበብና በፈጠራ ዳይሬክሽን የጀመረ ሲሆን፣ በኋላ ወደ ፎቶግራፍና በፋሽን የሚመሩ የምስል ትረካዎች ተሸጋግሯል።
ኦቦቺ የራሷ ተሞክሮ ከሌሎች ኤልጂቢቲኪው+ ናይጄሪያውያን ተሞክሮ የተለየ መሆኑን ጠንቅቃ ታውቃለች። “በቀላሉ የተቃራኒ ፆታ ሴት መስዬ ላልፍ እችላለሁ” ስትል ታስተውልላች። ይህ በአንፃራዊነት የማይታይ ማንነቷ፣ ሌሎች ከሁለትዮሽ ስርዓተ-ፆታ ውጪ የሆኑና የፆታ ማንነታቸው በግልጽ የሚታዩ ሰዎች ከሚገጥማቸው አንዳንድ ከባድ እውነታዎች ሳይጠብቃት እንዳልቀረም ታመላክታለች።
ሆኖም በዚህ ሽፋን ጀርባ ከመደበቅ ይልቅ፣ በሥራዎቿ ውስጥ ማንነቷን አጉልታ ለማሳየት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመረጠች መጥታለች። ፎቶግራፍንና ሌሎች የፈጠራ መግለጫ ዘዴዎችን በመጠቀም፣ ስለ ኩዊርነት፣ ሴትነትና ግለሰባዊ ማንነት ላይ የሚነሱ የተዛቡ ግምቶችን በፀጥታ ትሞግታለች። ኦቦቺ ታይነት ለሌሎች ሰዎች ምን ያህል በፍጥነት ወደ አደጋ ሊቀየር እንደሚችልም በጥልቅ እንደምትገነዘብ ትናገራለች። “ማህበረሰቡ ሴታዊ ባህሪ ያላቸውን ወንዶች እንዴት እንደሚይዝ አያለሁ። ሰዎች ክፉ፣ ጨካኝና ጥቃት አድራሽ ሊሆኑ ይችላሉ።”
ይህ ግንዛቤ፤ በሥራዎቿ ውስጥ በምታነሳቸው ስሜታዊና ፖለቲካዊ ጭብጦች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ትገልጻለች። “አብዛኛው ሥራዬ የወንዶችን የበላይነት ሥርዓት በመጋፈጥ ላይ የሚያተኩረው ለዚህ ነው” በማለት ታስረዳለች። “በዙሪያዬ ያለውን ነገር እገነዘባለሁ፤ ስለዚህም ሥነ ጥበቤን ተጠቅሜ ይህንን ለመሞገት እጥራለሁ።”
ይህ ግንዛቤ፤ በሥራዎቿ ውስጥ በምታነሳቸው ስሜታዊና ፖለቲካዊ ጭብጦች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ትገልጻለች። “አብዛኛው ሥራዬ የወንዶችን የበላይነት ሥርዓት በመጋፈጥ ላይ የሚያተኩረው ለዚህ ነው” በማለት ታስረዳለች። “በዙሪያዬ ያለውን ነገር እገነዘባለሁ፤ ስለዚህም ሥነ ጥበቤን ተጠቅሜ ይህንን ለመሞገት እጥራለሁ።”
ከልዩነት ጋር ማደግ
ኦቦቺ ፎቶግራፍን ከማግኘቷ ከረጅም ጊዜ በፊት ከተለመደው በጥቂቱም ቢሆን የተለየች መሆኗን ተገንዝባ ነበር። በአቡጃና በአዳሪ ትምህርት ቤት መካከል እያደገች፣ በኢኑጉ ግዛት ወደምትገኘው ንሱካም አዘውትራ እየተጓዘች፣ በዙሪያዋ ስላለው ዓለም ከፍተኛ የማወቅ ጉጉትና ነገሮችን ለመረዳት የማያቋርጥ ፍላጎት እንደነበራት ታስታውሳለች።
“በልጅነቴ ለመማር በጣም ጉጉት ስለነበረኝ ብዙ ጥያቄዎችን እጠይቅ ነበር” በማለት ታስታውሳለች። “በጣም ብዙ አነብ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ በቀን አራት መፃህፍት እስከማንበብ እደርስ ነበር። ብዙውን ጊዜም በፍቅር ልብ ወለዶች ውስጥ ሰምጬ እጠፋ ነበር።” “አሁን ግን ያንን ችሎታ አጥቻለሁ” ስትል በለስላሳው ፈገግታዋ ታወጋላች።
ከአራት ወንድማማቾችና እህታማማቾች ታላቋ እና በኢግቦ ቤተሰብ የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ — እሷ ራሷን እንደምትገልጸው “አዳ” የሆነችው ኦቦቺ፣ ኃላፊነት የመውሰድ ስሜትና በራስ መተማመን እንዲኖራት ተደርጋ አድጋለች። ይህንንም በአብዛኛው ጠንካራና በሕይወቷ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላት ሰው አድርጋ የምትመለከታት እናቷ ቀርጻዋለች። ..
ኦቦቺ ስለ ልጅነቷ በፍቅር ትናገራለች፤ ትውስታዎቿም በአፍሪካ ከኤልጂቢቲኪው+ ሰዎች ሕይወት ጋር በተደጋጋሚ ከሚያያዙት የቤተሰብ መለያየትና መገለል ታሪኮች ጋር የሚቃረን ተቀባይነት አላቸው። አስተዳደጓን የተረጋጋ፣ በፍቅር የተሞላና በቤተሰብ ግንኙነት ላይ ጥልቅ መሠረት ያለው እንደነበር ትገልጻለች። እንዲያውም ከወላጆቿ ቤት የወጣችው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ፣ እሷና የፍቅር አጋሯ ከቤተሰቧ ቤት ብዙም ባልራቀ አካባቢ የራሳቸውን መኖሪያ ካገኙ በኋላ ነው።
ብዙ ኤልጂቢቲኪው+ ሰዎች መገፋት፣ ጥቃት፣ ከቤተሰብና ከቅርብ ሰዎች መራቅ ወይም ማንነታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲደብቁ የሚደረግባቸው ጫና ቢያጋጥማቸውም፣ ኦቦቺ ከቤተሰቧ ጋር ያላት ግንኙነት በድጋፍና በመደራደር መካከል ባለ ውስብስብ ሚዛን የተቀረጸ ነው። ምናልባትም ይህ ውስብስብነት፣ በማህበራዊ ወግ አጥባቂነት የምትታወቀውን ነገር ግን ቀስ በቀስ እየተለወጠች ያለችውን የናይጄሪያ ማህበረሰብ እና በውስጡ ያለውን ኩዊርነት የምትመለከትበትን መንገድ ሳይቀርፅ አይቀርም።
ኦቦቺ በልጅነቷ ዘመን ስለ ኩዊርነት በንቃት በማሰብ ብዙ ጊዜ እንዳላሳለፈች ትናገራለች። የወሲባዊ ዝንባሌዋንና ይህ በናይጄሪያ ማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ ምን ማለት እንደሆነ ግን በይበልጥ መረዳት የጀመረችው፣ በ19 ዓመቷ ዩኒቨርሲቲ እያለች ነበር።
“ያደግሁት ወጣት ሴቶች የወንዶች ሚስት ለመሆንና ከእነሱ ጋር ቤተሰብ ለመመሥረት እንዲመኙ በሚያስተምር ማህበረሰብ ውስጥ ነው። በውስጤ ግን ከሌሎች የተለየሁ መሆኔንና ለሕይወቴ የምፈልገው ያ እንዳልሆነ አውቅ ነበር።”
ከጊዜ በኋላ፣ ኦቦቺ በውስጧ በደመ ነፍስ የምትረዳው የልዩነት ስሜት፣ በራሷ ቃላትና አረዳድ መግለፅ ወደምትችለው ማንነት ተለወጠ።
“ኩዊር የሚለው ቃል በራሱ መንገድ ‘የተለየ’ ማለት ይመስለኛል። ‘ልዩ’ ማለት ነው” ትላለች ኦቦቺ፤ ምንም እንኳን ዳግም በአዎንታዊ ትርጉም ጥቅም ላይ የዋለው ይህ ቃል በሁሉም የኤልጂቢቲኪው+ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላገኘ ብትገነዘብም። “ለእኔ፣ በዓለም ውስጥ ከሌሎች በተለየ መንገድ እንደምኖርና እንደምጓዝ ያመለክታል።”

አሌክሳንድራ ኦቦቺ በረጋ እንቅስቃሴዎች፣ በጋራ ቦታዎችና በቅርበት በተሞሉ አፍታዎች አማካኝነት፣ ለታይታ ያልተሠሩ ቢሆኑም ጥልቅ ስሜታዊና ፖለቲካዊ ትርጉም ያላቸውን ግንኙነቶች በፎቶዋ ትመዘግባለች።
እውነተኛ ማንነትዎ ተቀባይነት የሚያገኝባቸውን ቦታዎች መፈለግ
ኦቦቺ አንዳንድ ጊዜ በኦንላይን አሉታዊ ነገሮች ቢያጋጥሟትም — በናይጄሪያ የፋሽንና የፈጠራ ዘርፎች ውስጥ ያሉትን ጠባብ የውበት መለኪያዎች የምትሞግት ትልቅ የሰውነት ቅርጽ ያላት ሴት በመሆኗ የሚቀርብባትን ትችት ጨምሮ — እነዚህ ነገሮች ሕይወቷን እንደማይመሩት አጥብቃ ትናገራለች።
“በኦንላይን የሚከሰቱ ነገሮች፣ ስሜቴን እንደ መመሪያ በመጠቀም ሕይወቴን የምመራበት መንገድ ላይ ብዙም ተጽዕኖ አያሳድሩም” ትላለች ኦቦቺ። በጂም ውስጥም ሆነ ከጓደኞቿ ጋር፤ ራሷን የተረጋጋችና ከእውነታው ጋር የተገናኘች ሆና እንድትቆይ የሚረዷት ቀላልና የተረጋጉ ልማዶች እንዳሏትም አክላ ትገልፃለች። “ለእኔ ከሁሉም በላይ አስፈላጊዎቹ፣ በእውነተኛ ሕይወቴ ውስጥ የምገነባቸው ግንኙነቶችና የማገኛቸው ተሞክሮዎች ናቸው።”
የኤልጂቢቲኪው ማንነትን ይዞ በግልጽ መኖር የተለያዩ አደጋዎችን ሊያስከትል በሚችልበት ማህበረሰብ ውስጥ ኦቦቺ ግንኙነቶቿን በጥንቃቄና በዓላማ ትመርጣለች። “በጣም ተግባቢ ሰው ብሆንም፣ ጓደኞችን በመምረጥ ረገድ በጣም ብልህና ጥንቁቅ መሆን እንዳለብህ አምናለሁ” በማለት ትገልፃለች። “ከጓደኞችህና ከምታውቃቸው ሰዎች ጋር ስትሆን ደኅንነት ሊሰማህ ይገባል።”
“የሥነ-ጥበብ መድረኮች በአብዛኛው የበለጠ ተቀባይ አስተሳሰብ ያላቸው ይሆናሉ” ስትል ታክላለች። “ራስን ለመግለጽ፣ ለመመርመርና ሰዎች ከጠባብ ማህበራዊ ግምቶች ውጭ ሆነው እንዲኖሩ የሚያስችል ቦታ አለ።”
ከጊዜ በኋላ፣ አብዛኞቹ የኦቦቺ የቅርብ ግንኙነቶች የተመሠረቱት በፈጠራ መድረኮች ውስጥ ሲሆን፣ በትብብር፣ በመተማመንና ራስን በነፃነት ለመግለጽ ባላቸው የጋራ ቁርጠኝነት ተቀርፀዋል።
“አሌክዛንድራ የግል የሆነውን ተሞክሮ ሁሉም ሰው ሊረዳውና ሊገናኝበት ወደሚችል ነገር የመቀየር ብርቅዬ ችሎታ አላት” ይላል የፈጠራ ዳይሬክተርና የረጅም ጊዜ የሥራ አጋሯ ካዮዴ። “እይታዋ በሐቀኝነቱ፣ በጥልቀቱና ረቂቅነትን ለመጠቀም ባለመፍራቷ ለየት ይላል። የግል ስሜትንና ሰፊ ማህበራዊ ተጽዕኖን በአንድ የሚያስተሳስር፤ የራሷ መሆኑ የማያጠራጥር የሥነ-ጥበብ ስብስብ ለመፍጠር
ከኦቦቺ ጋር የሠሩ ሌሎች ሰዎችም በሥራ ወቅት የምትፈጥረውን ድባብ ይጠቅሳሉ። በመጀመሪያዎቹ የፎቶ ቀረፃዎቿ በአንዱ ላይ የተባበረችው ሞዴል ዮላንዳ፣ “ልዩ ራዕይ/ዕይታ ነበራት፣ ያንንም በሐሳቧ እንዳለው በትክክል ዕውን ለማድረግ ትጠነቀቅ ነበር፤ [ነገር ግን] ከልብ ደግ ነበረች፣ [እና] ሁሉም ሰው እውነተኛ ማንነቱን በነፃነት እንዲገልጽ በእውነት ቦታ ትሰጥ ነበር፣” በማለት ታስታውሳለች።

ለስላሳነትንም ይሁን ጥንካሬን፣ ጸጥታንም ይሁን ተቃውሞን ብትቀርጽም፣ የአሌክሳንድራ ኦቦቺ ምስሎች ስለ ፆታ፣ ስለ ሰውነትና ስለ ባለቤትነት የተለመዱ ዋነኛ ትርክቶችን ይሞግታሉ።
የወደፊቱን በምስል ማስቀረት
በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ እያገኘች ያለችው እውቅና እያደገ ቢመጣም፣ ኦቦቺ አሁንም የፎቶግራፍ ጥበቧን የበለጠ በማዳበር ላይ አተኩራለች። “በአሁኑ ወቅት፣ ሁልጊዜ ስነግራቸው የነበሩትን ታሪኮች ነው አሁንም እየነገርኩ ያለሁት” ትላለች። “ነገር ግን የራሴን ድምፅ እንዴት የበለጠ ማጥራት፣ ምስሎቼን ማሻሻልና እንደ አርቲስት ማደግ እንደምችል ላይ እያተኮርኩ ነው።” ከካሜራው ጀርባ ያለው ሰው፤ ፎቶ ከሚነሱት ሰዎች ጋር የአንድ ማህበረሰብ አባል ሲሆን፣ የሚያስከትለውን ተጨማሪ ኃላፊነት በሚገባ የተገነዘበች ትመስላለች።
ሌሎች ሰዎች እሷን እንደ ዓርዓያ መመልከታቸው ብዙም ደስ ላያሰኛት ቢችልም፣ ኦቦቺ ሥራዋ ከአገሯ ድንበር ባሻገር ተደራሽነትና ተፅዕኖ ያለው ባለተሰጥዖ አርቲስት ናት። ሥራዋ ይህን ያህል ቀልብ የሚስብበት ዋነኛ ምክንያት፣ በማህበረሰቡ ዳር የተገፉ ሰዎችን የጋራ ታሪክ ዋና ገፀ-ባህሪያት የማድረግ ችሎታዋ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጊዜም ማንነታቸውን ወደ ቀላልና ጠባብ ትርክት ሳትቀንስ፣ ገራገርነታቸውንና ጥንካሬያቸውን አጣምራ ማሳየቷ ነው።
የኤልጂቢቲኪው ማህበረሰብ አባላት ወይም ትልቅ የሰውነት ቅርጽ ያላቸው ሴቶች በስራዋ ሲሳተፉ፣ ማህበረሰቡ በላያቸው ከሚጭናቸው ግምቶችና ገደቦች፣ ራሳቸውን ለመግለፅ የበለጠ ኃይልና ነፃነት ተስምቷቸው እንዲሄዱ ኦቦቺ ተስፋ ታደርጋለች። በዚህ ዓመት መጨረሻ ለማሳተም እያቀደች ላለው የፎቶ መጽሐፍ መነሽ ከሆኑላት ምክንያቶች አንዱም ይህ ነው።
“በቻልኩት መጠን ተፅዕኖ ማሳደሬን መቀጠል እፈልጋለሁ” ትላለች፤ ቅንነት በተሞላው እና ይህንኑ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ መወሰኗን በሚያስተማምነው ድምፅዋ። “በሥራዬ አማካኝነት ታይተናል፣ ተወክለናል የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ማወቄ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው። በተለይም ራሳቸውን በዚህ መልኩ ሲወከሉ ማየት ያልለመዱ ሰዎች።”
ለአሌክዛንድራ ኦቦቺ፣ ማንነቷን በግልጽ የምትኖር ኩዊር የፎቶግራፍ ባለሙያ መሆን፣ የኤልጂቢቲኪው ታይነትን ከማሳደግ ባሻገር እጅግ የላቀ ትርጉም አለው። ይህ፣ የፈጠራ ድንበሮችን በመግፋት፣ ራሱን ከሌሎች የተለየ ሆኖ ለተሰማው ማንኛውም ሰው፣ ብዙውን ጊዜ እንዲጠፋና እንዳይታይ በሚጠብቅ ማህበረሰብ ውስጥ የበለጠ በነፃነት የሚኖርበትን ቦታ ስለመፍጠር ነው።

አሌክሳንድራ ኦቦቺ የማህበረሰቧን ውበት፣ ውስብስብነትና ፅናት የሚያረጋግጡ አማራጭ ማህደሮችን ለመገንባት ትጥራለች።

