ቺማኖ ግለሰባዊነቱን እና የቲያትር ችሎታውን ተላብሶ — ፋሽኑ፣ እራስን የመቀበል መልዕክቱን እና ይቅርታ የማይጠይቅ የኤልጂቢቲኪው+ ታይታነቱን የሚያጎላ ነው። ፎቶግራፍ፡ በዊሊስ ቺማኖ የቀረበ
የቀድሞው የሶቲ ሶል ባንድ አባል ራሱን ከሚስጥር ማንነቱ ወደ ነፃነት ያደረገውን ጉዞ እና ለምን የኤልጂቢቲኪው ዓርዓያ ሆኖ በመታየቱ ቢደሰትም ግን አንዳንዴ አስመሳይ እንደሆነ እንደሚሰማው ያንጸባርቃል
በቤዛ ለዓለም
በአህጉሪቱ በነበራቸው የሁለት ዓስርተ ዓመታት የሙዚቃ ጉዞ ቆይታ፣ እንደ ሶቲ ሶል ከባድ የባህል ተፅዕኖ ያሳደሩ የአፍሪካ የሙዚቃ ስራዎች ጥቂት ነበሩ። የኬንያው ኳርቴት፣ በለሰለሰው ቅላፄያቸው፣ እና የቅኝት ዘውጎችን ቀላቅሎ በያዘው ድምፃቸው፣ ከሚማርከው ስብዕናቸው እና በልዩ የስዋሂሊ የራስ መተማመን ድባብ ጋር በማዋሃድ፣ የምስራቅ አፍሪካን አፍሮ-ፖፕ ሙዚቃ በልዩ መንገድ ለመቅረፅ ችለዋል። ለአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ትርዒት ማቅረብ ይሁን፣በአውሮፓ እና በአፍሪካ የኤምቲቪ ሙዚቃ ሽልማቶችን ማሸነፍ፣ ይህ የሙዚቃ ቻርቱን የተቆጣጠረው ባንድ ከሌጎስ እስከ ለንደን ድረስ ሙሉ ቲኬቶችን ለሸመቱ ታዳሚዎች በመጫወት ድንበርን ለመሻገር ችለዋል።
ሆኖም ለዚህ ባለ ሙሉ ሃይል ባንዱ አንድ አራተኛ አቀንቃኝ እና እጅግ ማራኪ አባል ዊሊስ ቺማኖግን፣ ከመድረክ ጀርባ ያለው ህይወቱ የትኛውም ግጥም ሰንጥቆ ሊያስተላልፍ ከሚችለው በላይ በፀጥታ የተሞላና ድብቅ ነበር። በማህበረሰቡ ዘንድ የተቃራኒ ፆታ አፍቃሪ ወንዶች ባንድ ስብስብ ተደርጎ በሚታየው በዚህ ቡድን ውስጥ፣ ቺማኖ በመድረክ ላይ ልዩ ድምቀትን እየተላበሰ ቢወጣም፣ ፆታዊ ማንነቱን በመደበቁ በግሉ ከፍተኛ ትግልን አድርጓል። “[ይህን] ለመደበቅ የተቻለኝን ሁሉ ማድረግ ነበረብኝ” ሲል በኋላ ላይ አስታውሷል።.
ከዘናጭ፣ ማራኪና እና በራስ መተማመን ከተላበሰው ወጣት ሙዚቀኛ ጀርባ፣ የግል እውነታውን ሚስጥር አድርጎ ማቆየት ብቻ ሳይሆን ይታገል የነበረው፣ ነባራዊው ሁኔታው የሚያስከትለውንም አደጋ ነበር። ኬንያ ኤልጂቢቲኪው+ ሰዎችን ወንጀለኛ ከሚያደርጉ 32 የአፍሪካ አገሮች አንዷ ስትሆን፤ በተስማሙና በተፈቃቀዱ ሰዎች መካከል የሚደረጉ የተመሳሳይ ፆታ ፆታዊ ድርጊቶችን እስከ 14 ዓመት በሚደርስ እስራት ትቀጣለች። ይህ የቅኝ ግዛት ዘመን ህግ፣ ዘመቻ አራማጆች ለመሻር የሞከሩት ቢሆንም የከፍተኛው ፍርድ ቤት የክስ ጥያቄውን በ2019 ውድቅ አድርጎታል።

ከሶቲ ሶል ባንድ ጋር፤ ቺማኖ መሃል ላይ መድረኩን ሲመራ — በኋላ ላይ መድረኩን እውነቱን እና የኩዊር ሐሴትን በሚያከብር ሙዚቃ ተቆጣጥሯል። ፎቶግራፍ፡ በዊሊስ ቺማኖ የቀረበ
ዝናው፤ እያንዳንዱን የግል ትግል ያጎላው ቺማኖ፣ የምስጢሩ ክብደት እጅግ የላቀ ነበር። የግል ፆታዊ ማንነቱ ያለፈቃዱ በመጨረሻ ሲጋለጥ፣ በራሱ ፍላጎት ሊገልጠው ያቀደውን እውነት እንዲጋፈጥ አስገድዶታል። ነገር ግን ያልተፈለገ ግምትን ከመሸሽ ወይም ከመካድ ይልቅ፣ በኬንያ አንድም የፖፕ ሙዚቃ ኮኮብ ያልፈፀመውን አድርጓል። እ.ኤ.አ. በታህሳስ 2021፣ በብሔራዊ ጋዜጣ ላይ በመውጣት የተመሳሳይ ፆታ ወንድ አፍቃሪ መሆኑን ይፋ አደረገ።
"ሁሉንም ነገር ግልፅ አድጌዋለሁ፤ ከአሁን ጀምሮ ሃኩና ኩጂፊቻ ጂፊቻ (መደበቅ ያበቃል)። ፆታዊ ማንነት ብቻ አንተን አይገልፅም። ይህ እኔ ራሴን፣ የፈጠራ ሥራዬን፣ ይፋ አድርጌ እና በእውነትኛ ማንነቴ መኖሬ ብቻ ነው" ሲል 'የዜናውን እፍታ ለማጋራት እድሉን ላገኘው ሪፖርተር ተናግሯል።
ዜናው በፍጥነት በዓለም ዙሪያ ተሰራጨ። ከቢቢሲ አርዕስተ ዜናነት አንስቶ እስከ ባንዱ ሶስት ሚሊዮን የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ድረስ ዜናው አነጋጋሪ የነበረ ሲሆን፤ ኮከቡን በቅንነቱ እና በጀግንነቱ ሰላምታ የሰጡ የታዋቂ ግለሰቦች፣ የአክቲቪስቶች እና የአይን እማኞችን የድጋፍ ማዕበልም ፈጥሯል። አንዳንድ አድናቂዎች ቺማኖን ሲያሞግሱት፣ ሌሎች ደግሞ በአገር ውስጥ እና በአጠቃላይ በአህጉሩ ውስጥ በግልፅ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ አፍሪካዊ ሙዚቀኛ ላይ ጥላቻን ለመንዛት እድሉን ተጠቅመዋል። በወቅቱ ሲናግር፣ "በጣም ብዙ ጥላቻ ነበር። ኦ አምላኬ፣ በጣም ብዙ" ብሎ ነበር።
ምንም እንኳን ይህ ለውጥ በአብዛኛው ነፃ የሚያወጣ ቢሆንም፣ ሕይወት ግን ዳግመኛ አንድ ዓይነት አልሆነም። አንዳንድ ጊዜም ደግሞ አሳዛኝ ነበር። ምንም እንኳን እጅግ ያሳሰበውና ያስከፋው ፍርሃቱ ባያልፍም፤ ሶቲ ሶል ባንድ አልፈረሰም፤ የግሉ የጥበብ ስራውም አልተቋረጠም። ቺማኖ ራሱን ይፋ ካደረገ በኋላም ባንዱ ከሙሉ አባላቱ ጋር ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት መጫወቱን ቀጥሏል። ባንዱ መጫወት ባቆመበትም ጊዜ፣ ቺማኖ ነጠላ ዜማውን አስቀድሞ ለቋል። የባንድ ባልደረቦቹ - ሳቫራ ሙዲጂ፣ ፖሊካርፕ ኦቲዬኖ እና ቢየን-አይሜ ባራዛ ያላሰለሰ ድጋፍ ብዙዎች እንደ አጋር እንዲመለከቷቸው አድርጓቸዋል።
የቺማኖ እንደ አርቲስት መቀጠል እና በኋላም የስኬቱ ጉዞ ዋስትና አልነበረውም። ኬንያ በምስራቅ አፍሪካ ለሚኖሩ ኤልጂቢቲኪው ሰዎች በጣም አደገኛ ከሚባሉት ሀገራት አንዷ ባትሆንም፣ አሁን ባላት የፀረ-ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ህግ፣ ክሶች እምብዛም የማይታይበት እና የህዝብ አመለካከቶች ከኡጋንዳ እና ከኢትዮጵያ የተሻለ ተደርጎ ቢወሰዱም፣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆን አሁንም ቢሆን በወንጀል የሚያስጠረጥር አልፎም ለአዳጋ የሚያጋልጥ አሳዛኝ ተሞክሮ ሊሆን ይችላል። የታዋቂ ሰዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ልዩ መብት እና ቦታ ላልተፈለገ አደጋ እና ስውር የሆኑ ዓድሎዎች ያጋልጣል። እ.ኤ.አ. በ 2022 የናይሮቢ ፖሊስ የቺማኖን ላቭ እና ሃርሞኒ የተሰኘ ኮንሰርት “የደህንነት ምክያቶችን” በመጥቀስ ሰርዟል። ይህም በብዙዎች ዘንድ በይፋ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ የሆነን ሙዚቀኛ ሳንሱር እንደማድረግ ተወስዷል።
የ ‘ፋሚሊ ፕሮቴክሽን ቢል 2023’ ን በመደገፍ"ከተመሳሳይ ፆታ ግንኙነቶችን ጋር የተገናኘን ማንኛውንም ነገር ለመከልከል"በሚፈልጉ ፖለቲከኞች የኬንያ የአየር ንብረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቢመጣም፤ ቺማኖ ማንነቱን ተቀብሎ በድፍረት መናገር ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ሙዚቀኛው እራሱን በአህጉሪቱ ውስጥ በኤልጂቢቲኪው ማንነት ዙሪያ ያሉ ፈታኝ ጉዳዮችን ከሚሞግቱ ጥቂት ታዋቂ ሰዎች መሃል ለሞሆን ችሏል። በሶቲ ሶል የመጀመሪያዎቹ ዓመታት “የቡድኑን ትልቅ የመሆን እድል እንዳይበላሽ”“ጭንብል ለብሻለሁ”ያለው ሰው፣ በግልፅ የሚታይ ዓርዓያ እና ቀንደኛ ተሟጋች ሆነ።
የቺማኖ የግል የሙዚቃ ስራ ቻርቱን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር፣ ከሶቲ ሶል የጋራ ማንነት አልፎ በድፍረት የግል ማንነቱን ለመዳሰስ ችሏል። ሄቪ ኢዝ ዘ ክራውን (Heavy Is the Crown) በተሰኘው የመጀመርያው የጥቂት ሙዚቃዎች አልበም ስብስ እና እንደ ፍራይደይ ፊሊኒግ (Friday Feeling)ባሉ ነጠላ ዜማዎች የተከፈተው አዲስ ምዕራፍ፣ በግል ማንነት፣ ራስን መውደድ እና የነፃነት ጭብጦች ላይ የሚያቀነቅኑ ሲሆን፤ ሙዚቃዎቹም እንደ ውይይት እና መግባቢያ ሆነው ያገለግላል። ለቺማኖ፣ እያንዳንዱ ዘፈን በአንድ ውስን ቦታ ውስጥ ለመቆለፍ ፈቃደኛ አለመሆን እና ህጉ መኖር እንደሌለበት በሚያስገድድባቸው ቦታዎች እንኳን ደስታን እንደሚያንሰራራ የሚያሳይ የምስክርነት መግለጫ እና የአይበገሬነት ተምሳሌት ነው።

ቺማኖ የተዋበተ የፒች ልብስ ለብሶ — የብቸኛ አርቲስነት ዘመኑን የሚያንፀባርቁ በራስ የመተማመን እና ችሎታን ማሳያ። ፎቶግራፍ፡ በዊሊስ ቺማኖ የቀረበ
ያ ዝግመተ ለውጥ፣ “ቺማኖ ላይቭ! ሄቪ ኢዝ ዘ ክራውን፡ ኤ ዋን ማን ሾው” በተሰኘው በአፍሪካ ሴንተር የቻኩላ ፕሮግራም ድጋፍ እየተካሄደ ባለው የዩኬ-ኬንያ የባህል ወቅትበቀረበው የቺማኖ የቅርብ ጊዜ የለንደን ኮንሰረት ለመመስከር ተችሏል። በትርኢቱ፣ ሙዚቃዎቹን ከአዝናኝ ታሪኮችና እና የግል ልምዶች እያዋሃደ፣ አንድም የግል የሙዚቃ እድገቱን በሌላ ጎኑ ደግሞ በአህጉሪቱ በጎ ተፅዕኖን ለምፍጠር ለሚሻ አዝናኝ ኤልጂቢቲኪው አርቲስት ወሳኝ ጊዜ ነበር።
ጨዋታችንም የጀመረው፣ ሙዚቃን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ራስን ለመግለጽ እና በህይውት ለመቀጠል ብቻ ሳይሆን፣ ለተቋሞ እና ለነፃነት እንዴት እንደተጠቀመበት በመወያየት ነበር።
ቺማኖ፤ ፍፁም ግልጽነት በተሞላው፣ ስሜታዊ ስብስቡን በአስቂኝ ወጎቹ እያዋዛ፣ ከሶቲ ሶል አስደማሚ ዝና አንስቶ እስከ እራስን የመቀበል ጥልቅ ግላዊ ተጋድሎዎቹ ድረስ የነበረውን የስራ ዘመኑን ያካፈለኝ። ውጤቱ ደግሞ አንድ አርቲስት ህይወቱን በትክክል ለመኖር ሲማር የሚያሳይ ምስል ብቻ ሳይሆን፣ በህዝብ ዘንድ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ አፍሪካዊ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ሰፋ ያለ ነፀብራቅ ነበር።
ተጋላጭነትን ወደ ታይታነት እና ቅላፄን ወደ ፅናት በመቀየር፣ ቺማኖ አርቲስቶች ከሚፈጥሩት ስራ ወይም ከማዝናናት ባለፈ የሚያበረክቱት ብዙ እንዳለ ያስታውሰናል።
እንኳን ወደ ፋጤ በደህና መጣህ።
ስለ ጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
ስለ ፈጠራ ሥራህ ሂደት ንገረን። ሙዚቃህ ድንገት በሚመጣ እሳቤ የሚወለድ ነው?
አሁን ብቸኛ አርቲስት በመሆኔ አዳዲስ ልምዶችን ማካተት ነበረብኝ። ከቡድኑ ጋር፣ የፈጠራ ችሎታችንን የሚቀርፁ አንዳንድ ልምዶች እና ሥርዓቶች ነበሩን። በግሌ ግን የራሴን መንገድ መፈለግ ነበረብኝ። ለኔ ዝምታ ወሳኝ ነው። እራሴን በመንፈሳዊ መንገድ መፈለግ፣ እራሴን ማረጋጋት እና የሚያበረታቱ ቃላቶችን ደጋግሞ መጥራት፣ ወደ ፈጠራ ዞን የምገባበት መንገድ ነው። አንዳንድ ጊዜ ያ ማለት፣ አንድ ሃሳብ በስልኬ ላይ መቅዳት፣ አንዳንዴ ደግሞ ፀጥ ባለ ቦታ ላይ ተቀምጦ ማሰብ ሊሆን ይችላል።
ራስህን ይፋ ካደረክ በኋላ፣ ፍራይ ዴይ ፊሊንግ የተሰኘው ነጠላ ዜማህ የማንነትህ “እውነተኛ መገለጫ” ነው ብለህ ነበር። ለምን ነበር? ዘፈኑን ለመስራት ያነሳሳህስ ምንድን ነው?
ዜማው በህልሜ ከመጣው ዘፈኖች መካከል አንዱ ይሄ ነው። አስታውሳለሁ። ከእንቅልፌ ነቃሁ እና ወደ ጓደኛዬ ወለል ሄድኩ፣ እና ድምጹን ከፍቼ መዝፈን ጀመርኩ። እኔ ሁልጊዜ የ 80 ዎችን ፓንክ፣ ሮክ-ስታር እና ዲስኮ ዘመንን እወዳለሁ። በጣም ነፃ አውጪ ነበር። ፍራይዴይ ፊሊንግ ማለት ያ ነው። “ራሴን ነፃ እያወጣሁ ነው” እና “ለባለሥልጣናት ደውሉ” የሚሉት ግጥሞች እንኳ፣ ‘ምን እንደማደርግ ታውቃላቹህ እናም ልታስቆመኝ አትችሉም’ የሚሉ ናቸው።
በባንዱ ውስጥ ከቆየሁ በኋላ፣ አንድ ነፃ የሚያዋጣ፣ የመጀመሪያ ነጠላ ዘፈን የሚያስፈልገኝ ያህል መስሎ ተሰማኝ።…ኦ-አምላኬ- ነፃ የሚያወጣ ዘፈን አስፈልጎኝ ነበር።
መልካም ሀሳቦች ብዙውን ጊዜ በሕልማችን ይመጣሉ።
አዎ፣ ይመጣሉ።
በዚህ ተመሳሳይ ዘፈን ላይ "ቺማኖ ማን እንደሆነ እና ይህም ለመሸከም የሚከብድ ዘውድ እንደሆነም በትክክል ማወቅ እንደምንችል ተናግረሃል"። ያ የነፃነት ጊዜ ምን ይመስል ነበር?
የአንድ አፍታ ነበር ማለት አልችልም። በጊዜ ሂደት የመጣ ነው። በራሴ ላይ ብዙ የምሠራው ሥራ ስለነበር የተለያዩ ደረጃዎች ነበሩት። በ 30 ዎቹ አጋማሽ ሁሉን እስከ መጨረሻው ድረስ ለማወቅ እችላለው ብዬ አስቤ ነበር፣ ግን አልቻልኩም። ደስ የሚለው ግን ራሴን ይህን ከማድረግ ግፊት ነፃ አውጥቻለሁ። ይህ ደግሞ ነፃ የሚያወጣ ነው። ሁሉንም ነገር አንድ ላይ ባለመሆኑ እራስህን ይቅር ማለት እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እራስህን መውደድ ነው።
ትኖራለህ፣ ትማራለህ፣ እናም ትቀጥላለህ። አሁንም እየሄድኩበት ያለው ጉዞ ይሄ ነው። እራሴ ላይ ጫና የምፈጥርበት ጊዜ ዘውዱ የሚከብድበት ጊዚያት ነበሩ፣ ነገር ግን አሁን በጣም የተሻለ ቦታ ላይ ነኝ። ሰው መሆን የሙከራ ሂደት እንደሆነ አይቻለሁ - ሁልጊዜም በሂደት ላይ ያለ ስራ ነህ።
ዘውዱ አሁን ምን ያህል ከባድ ነው?
በጣም ቀላል ነው። በዚህ ሁሉ መጨረሻ ላይ፣ ያንተን ውድቀት፣ ልምዶችሁን፣ እራስህን የምታይበትን ማንኛውንም ነገር መሸከም ነው። በህይወት ውስጥ እንዴት ፀጋ በተሞላው መንገድ እንደምትጓዝ ነው። ዓለምን እንዴት እንደምትመለከት ደግሞ ደጋግሞ መለወጥም ጭምር ነው። ከሞላ ጎደል አእምሮን ግራ የሚያጋባ ሊሆን ይችላል።
አንተ እንዴት ለሁኔታዎች ምላሽ እንደምትሰጥ እና እንዴት ለነገሮች መፍትሄ ማበጀት እንደምትችል ነው። ለዓለም ያለህ መሰረታዊ አመለካከት ነው። አንተን የሚደግፉ ሚሊዮን ሰዎች ሊኖሩህ ይችላሉ፣ ግን አንድ ሰው ትንሽ የሚያስከፋ ነገር ሲናገር ያ ከአንተ ጋር ተጣብቆ ይቆያል። ያንን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል፣ እይታህን እንዴት መቀየር እንደምትችል መማር አስደናቂ ነው።
ብዙዎች እንደ ኤልጂቢቲኪው ዓርዓያ አድርገው የሚያዩህ አንዱ ምክንያት ይህ ይመስለኛል። ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል?
ሰዎች በዚያ መንገድ ካዩኝ፣ አንድ ነገር በትክክል እየሰራሁ መሆን አለበት። ከአፍሪካ - በተለይም ከምስራቅ አፍሪካ - በግልፅ፣ በኩራት እና ያለ ሃፍረት በመኖሬ፣ አንዳንድ ምስጋናዎችን መውሰድ የምችል ይመስለኛል። ሌሎች እንድዚህ አይነት ውክልና እንደሚያስፈልግ እና፣ ራሳቸውን በእኔ ውስጥ ማየት እንደሚችሉ ያሳያል።
ምንም እንኳን ተመሳሳይ ሁኔታ ወይም ክልል እንኳን ባንጋራ፣ አንተን የሚመስል ሰው ማየት ‘እኔም ማድረግ እችላለሁ’ ብለህ እንድታስብ ያደርግሃል። ለእኔ፣ አንድ ሰው ሲገነባ ካየሁ፣ እኔም መገንባት እንደምችል የሚያሳይ መሰረትም ነው።
በቀደምት የሙያ ዘምንህ ወቅት ሽልማት አሸናፊ የኬንያ ባንድ አካል ነበርክ። ይፋ የመሆን ጉዞህን እንዴት ቀረፀው?
ዋው! በእርግጥ ትልቅ ተፅዕኖ ነበረው። መጀመሪያ ላይ ራሴን ለዓለም እንዴት እንደማቀርብ ተፅዕኖ ነበረው። ምናልባትም፣ በተወሰነ ደረጃ፣ ሙሉ በሙሉ ይፋ መውጣቴን አዘግይቷል። ግን ሁሉም ነገር በራሱ ጊዜ፣ አይደል?
በመጀመሪያ እንደ ሰው በቅጡ ስለ ፆታዊ ማንነቴ ማሰብ ከመጀመሬ በፊት፣ በራሴ ወደ ምተማመንበት እና ወደ ማምንበት ሁኔታ ላይ ለመድረስ ብዙ ጊዜ ፈጅቶብኛል። ምክንያቱም “ጥሩ ሰው ነው ግን ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ነው” እየተባልን ማንነታችንን እንድንለይ ተደርገን ተምረናል። ስለዚህ፣ አንተ ማንነትህን በግልፅና በጥልቀት ለመገንዘብ፣አንዳንድ ነገሮችን እንደ አዲስ መማር ተገቢ ነው።
አዎ፣ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ፣ ተቃራኒ ፆታ አፍቃሪ ወይም ሌላ ልትሆን ትችላላህ። ምንም ይሁን ምን - አንተን የሚገልፀው ይህ ብቻ አይደለም። የምታዋጣው ነገር አለህ፡ ግብር መክፈል፣ ህይወት መለወጥ እና የራስህ ህይወት መኖር። ዓለምን ካገኛሃት ቦታ የተሻለ የማድረግ ሃላፊነት። ያ በዕውነቱ ሂደት ነበር።
ስለ ኤልጂቢቲኪው ማህበረሰብስ?
በባንዱ ውስጥ ሳለሁ ሙሉ በሙሉ የማህበረሰቡ አካል አልነበርኩም፤ እና ህይወት ቀጠለች። ልክ እንደ እኔ ካሉ ሰዎች ጋር ለመሆን፣ እንደ እኔ ካሉ አስደናቂ ነፍሳት ጋር ለመሆን እንደገና እየተለማመድኩ በሚመስል ሁኔታ ላይ ነኝ። እና ይሄም ራሱን የቻለ ሂደት ነው። አንዳንድ ጊዜ በማህበረሰቡ ውስጥ አስመሳይ የሆንኩ መስሎ ይሰማኛል። አንዳንድ ጊዜም በጣም ወደ ኋላ እንደቀረው ይሰማኛል።
ለሌሎች ለመናገር ወይም ለማበርከት ከመሞከሬ በፊት፣ መጀመሪያ መማር የምፈልግበት ቦታ ላይ ነኝ። በሂደቱ ውስጥ፣ ስለራሴ የበለጠ እየተማርኩ ነው፤ ምክንያቱም በእውነት መማር እፈልጋለሁ። ከራሳችን ጋር በሰላም መኖራችን የሚጀምረው ከኛ ነው ብዬ አስባለሁ፣ ይህም አስደናቂ ነው።
ራስህን ይፋ ስታደርግ ማን ዓርዓያ ሆነህ? ድፍረቱንስ እንዴት አገኘህ?
ኦ ዋው! ሁልጊዜ ወደ ብዙ ጥልቅ የማሰላሰል ጊዜያት እገባ ነበር። ሆን ብዬ የራሴን ዓለም በጭንቅላቴ ውስጥ በመፍጠር፣ እራሴን በኩዊንስ ኮንሰርቶች ውስጥ እያጠመቅኩ፣ ፍሬዲ ሜርኩሪን እየተመለከትኩ እና እራሴን በነሱ ቦታ ላይ አስብ ነበር። በሙዚቃ ዝግጅታችን ወቅት ማይክራፎኔን የእሱን [ፍሬዲ ሜርኩሪን] እንዲመስል የጠየኩበት ጊዜም እንደነበር አስታውሳለው። እነዚያ ጊዜያት፣ እነደ ፍሬዲ ሜርኩሪ፣ ኤልተን ጆን እና ግሬስ ጆን ካሉ የተወሰኑ የኩዊር ኮከቦች ጋር በመንፈስ የተገናኘሁባቸው እና ለራሴ የኩዊር ውበትን ያጎናፀፍኩባቸው ጊዜያት ነበሩ።
ምንም እንኳን ፕሪንስ ኩዊር ባይሆንም፣ እኔ በሁሉም የሮክ-ስታር ሃያል ባህሪያቱ ጋር ተዛመድኩ። እንዲሁም ፍራንክ ኦሽን- ኦ አምላኬ፣ የእሱን መልካም ባህሪያት እና ራሱን እንዴት እንደሚያቀርብ ማየት እወዳለሁ። አዎ፣ በጭንቅላቴ ውስጥ፣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን መድረክ ላይ የራሴን ትዕይንቶች እፈጥር ነበር። መድረክ ላይ ስሆን፣ ራሴን በፋሽን ቀበርኩት፣ በተላያዩ አልባሳት እራሴን የምገልፅበት መንገድ፣ የእኔ ብቻ ነበሩ፣ የደስታዬ ምንጭች ሆነውኛል።
ራስህን ይፋ ስታደርግ በጣም ያስገረመህ የማን ምላሽ ነው? የባንድ ባልደረቦችህ ወይስ ቤተሰብህ?
የባንድ ባልደረቦቼ ሁሌም ይደግፉኛል። እንደውም እ.ኤ.አ. በ2009 “እሺ፣ እናውቃለን። እራስህን ብቻ ተንከባከብ፣ አሁን እንቅትጥል” ብለው የነገሩኝ እነሱ ነበሩ። ደህና መሆኔን ማረጋገጥ ፈልገው ነበር።
ከሁሉም አሉታዊ ምላሽ ውጪ፤ ብዙ ያስገረመኝ፣ አገር ቤት ያሉት ፊታቸውን ያላዞሩብኝ አድናቂዎቼ ነበሩ። ‘እሺ፣ በመጨረሻ፣ አሁን ያለገደብ ሙዚቃ ወደ መፍጠር መሄድ እንችላለን’ የሚሉ ነበሩ። እኔም ‘ኦ፣ እሺ፣ አመሰግናለሁ’ ብዬ ነበር።
ሌሎች ብዙ ነገሮች ላይ ማተኮር ትችላለህ፣ ነገር ግን አንተን የማያውቁ ሰዎች ለአንተ ያላቸውን ፍቅር ሲያሳዩ ትመለከታልህ። ይህን በማድረጋቸው ሊፈረድባቸው በሚችል ማህበረሰብ ውስጥ አሁንም ከጎኔ ቆመዋል። ያ አስገረሞኛል፣ እናም ለዛ በጣም አመስጋኝ ነኝ።
ህልውናቸው ወንጀል እና ማንነታቸው በማህበረሰቡ ውድቅ በሆነባቸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ወይም ኬንያ ባሉ ሀገራት ለሚገኙ የኤልጂቢቲኪው አርቲስቶች መልዕክትህ ምንድነው?
ከባድ እንደሆነ አውቃለሁ፣ ፈታኝም እንደሆነ አውቃለሁ። በተለይ በአዕምሮ እና በሁለንተናዊ ማንነቶ ላይ የሚያሳድረው ጫና። አንዳንድ ጊዜ ያበድክ ያህል ሊሰማህ ይችላል። ትክክለኛ ማንነትህን መኖር ሁሉንም ነገር ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። ህይወትዎን፣ ቤተሰብዎን፣ ስራህን። ግን አይዞህ በርታ። ባልህበት ቦታ ያንተ ምትለውን ማህበረሰብ ፈልግ። አንተን ለመደገፍ እና አንዱ ለሌላው ድጋፍ የሚሆኑ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸውን ግለሰቦች ለማግኘት ሞክር። የተቀረው በራሱ ይመጣል።
ቀስ በቀስ ነገሮች ይገለጣሉ። ከቅርፊት ውስጥ ዘለህ በመውጣት ትተጋለህ። ስለ እኛ ያለው አንድ ነገር ሀሳባችንን ወደ አንድ ነገር ስናተኩር፣ እናሳካለን። ዓለም ብዙ ጊዜ ደግነት የጎደለው ስለሆነ፣ 50 እጥፍ ጠንክረን እንሰራለን፤ ግን አሁንም እናሳካዋለን። የኔ የሚሉትን ማህበረሰቡን ያግኙ - የተቀረው በራሱ ይመጣል። እና ያስታውሱ፣ ለራሳችሁ ርኅራኄ ማሳየትም በጣም በጣም አስፈላጊ ነው።
አንዳንድ ጊዜ እርስዎን የሚያዘገዮት ወይም የሚጎዱት የእራስዎ ደም ነው፤ ስለዚህ በሚችሉበት ቦታ የኔ የሚሉትን ማህበረሰብ እና ቤተሰብ መፍጠር አለብዎት። ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ማረጋገጫ ያስፈልገናል ለትዕቢት ሳይሆን በቀላሉ ‘እዚህ ነኝ፣ የተወደድኩ ነኝ፣ ደህና ነኝ’ የሚለውን ለማወቅ። በአርቲስቲክ ችሎታህ፣ በፈጠራ ችሎታህ እና በሰባዓዊነትህ መድረስ የምትችልበት ክፍተኛ ቦታ እንዳለህ መገንዘብ አለብህ። ማህበረሰብ በእርግጠኝነት አስፈላጊ ነው።
የሁሉም ሰው ዘውድ ብዙም የማይከብድበት ቦታ እንደሆነ እገምታለሁ።
በትክክል። ምክንያቱም ሁሉም ሰው ተመሳሳይ አክሊሎችን ስለለበሱ።
በጣም አመሰግናለሁ።
ስለ ጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
ይህን ቃለ መጠይቅ አጠር እና ግልፅ ለማድረግ ሲባል ጥቂት ማስተካከያዎች ተደርገዋል።

