ተስፋዬ ይልማ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ፤ ለፀጥታው ምክር ቤት ንግግር ሲያደርጉ፣ ታህሳስ 2018
በምክር ቤቱ ከሚቀመጡት 47 አገሮች አብዛኞቹ፣ በኤልጂቢቲኪው ሰዎች ጥበቃ ላይ አተኩሮ የሚሰራ ኤክስፐርትን ለማቆየት ድም ሰጥተዋል። ነገር ግን ዘጠኝ የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ፣ 15 አገሮች በድምፅ ወድቅ አድርገውታል።
በቤዛ ለዓለም
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል የሆነችው ኢትዮጵያ፤ የተባበሩት መንግስታት አካል፣ የኤልጂቢቲኪው+ ሰዎችን ሰብዓዊ መብት ማስጠበቅ ላይ አተኩሮ የሚያገለግል ባለሙያ ሊኖረው ይገባል የሚለውን የውሳኔ ሃሳብ በመቃወም ድምፅ ሰጥታለች።
በሴኔ 30 የተካሄደው የድምፅ መስጠት ስርዓት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መዋቅር ውስጥ፣ በፆታዊ ተማርኮ እና በፆታ ማንነት (SOGI) ላይ የተመሰረተ ጥቃትን እና መድልዎን መላ ለማለት ታስቦ የተመደበውን፣ ልዩ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርት ስልጣንን ለማደስ አሳቢ ያደረገ ነበር።‘_‘ገለልተኛ ኤክስፐርት በሶጊ’_’በመባል የሚታወቀው እና በፆታዊ ተማርኮ እና በፆታ ማንነት ላይ አተኩሮ የሚሰረው፣ የምክር ቤቱ ገለልተኛ ኤክስፐርት ሚና በ2016 ተጀምሮ፣ በ2019 እና በ2022 በድጋሚ ታድሶ ነበር። በአሁኑ ጊዜ፣ የደቡብ አፍሪካ ምሁር ግሬም ሪድ ይህንን የስራ ድርሻም ይዘዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ላይ ከሚቀመጡት 47 አባል አገራት ውስጥ፣ 29ቱ በአብላጫ ድምፅ የዚህን ኤክስፐርት ሚና ለሶስት ዓመታት እንዲራዘም ሲደግፉ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ 15 አገራት ተቃውመዋል።
"ይህ ድምፅ ኢትዮጵያ ለመላው ዜጎቿ የሰው ህይወት ያለውን ዋጋ የማስከበር ግዴታዋን ለመወጣት አሻፈረኝ ማለቷን እንደቀጠለች ማሳያ ነው…ይህ ለኤልጂቢቲኪውአይኤ+ ኢትዮጵያውያን ምን ማለት እንደሆነ በቅርብ እናውቃለን። ይህ ማለት የኢትዮጵያ መንግስት ሆን ብሎ መንግስታዊ ባልሆኑ እንደ ቤተሰብ፣ ጎረቤቶች እና ማህበረሰብ በአጠቃላይ ወይም ከመንግስት ተዋናዮች ጥቃት ሊጠብቀን አልቻለም ማለት ነው" ብለው ነበር የፃፉት፣ የኢትዮጵያውያን እና የዓለም አቀፉ ዲያስፖራ ኤልጂቢቲኪአይኤ+ ሰዎች ተሟጋች ቤተ ጉራማይሌ፣ ዜናውን አስከትለው በ Instagram ገፃቸው ላይ ምላሽ ሲሰጡ።
"በአካልም ሆነ በአዕምሮ ጤና መዳረሻ አገልግሎት ላይ፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወታችን፤ ሙሉ ተሳትፎን እንዳናደርግ የታለመ መድሎዓዊ አሰራርን ማሳያ ነው። ዝም አንልም። ሀገራችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶቻችንን እስክትቀበል እና እስክታከብር ድረስ ጩኸታችንን እናሰማለን" ሲሉ ቤተ ጉራማይሌ አጠቃለዋል።
የውሳኔ ሃሳቡን ከተቃወሙ አገሮች ውስጥ አብላጫዎቹ በአፍሪካ፡- አልጄሪያ፣ ብሩንዲ፣ ኮትዲቯር፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋምቢያ፣ ማላዊ፣ ሞሮኮ እና ሱዳን ሲሆኑ የተቀሩት ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከእስያ (ኩዌት፣ ኳታር፣ ማልዲቭስ፣ ባንግላዲሽ፣ ቻይና እና ኢንዶኔዢያ) ናቸው። ሁለት የአፍሪካ ሀገራት ቤኒን እና ጋና ከኪርጊስታን ጋር የድምፅ ተዓቅቦ አድርገዋል።
ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ በምክር ቤቱ ውስጥ ለኤልጂቢቲኪው+ ሰዎች የተሰጠውን ሚና እንዲቀጥል ድምፅ የሰጡ ብቸኛ የአፍሪካ ሀገራት ሲሆኑ፣ ሌሎቹ አገራት በዋናነት በላቲን አሜሪካ፣ አውሮፓ እና ምስራቅ እስያ የሚገኙ ናቸው። በማንኛውም ጊዜ፣ ከ 193 የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ አባል አገራት 47ቱ ብቻ በጄኔቫ ላይ የተመሰረተው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ ከየክልሉ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ይመረጣሉ።
የውሳኔ ሃሳቡ በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት አካል በተሳካ ሁኔታ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ፣ ከበርካታ ሀገራት ተቃውሞ ቢገጥማቸውም፣ የዓለም አቀፍ የኤልጂቢቲኪው+ ተሟጋቾች ድምፁን እንደ ድል ወስደውታል።
የኢልጋ ዎርልድ ዋና ዳይሬክተር ጁሊያ ኢርት በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሲሰጡ. ፣ “በዓለም ዙሪያ ማህበረሰቦቻችን የታገሉለትን የለውጥ እድገት ለማፍረስ በሚሞክሩ ወግ አጥባቂ ኃይሎች ዘመን፣ የዚህ ስልጣን መታደስ የተስፋ ጭላንጭል ነው... ማንም ሰብዓዊ ፍጡር ጥቃት እና መድልዎ ሊገጥመው አይገባም - እና በአጭሩ ከዚህ የተለየ ነገር የለም።” ብለዋል። ኢልጋ፣ የዓለም አቀፍ ሌዝቢያን፣ ጌይ፣ ባይሴክሹዋል፣ ትራንስ እና ኢንተርሴክስ ማህበር፣ ከ 1,900 በላይ የሚሆኑ፣ ከ 160 አገሮች እና ግዛቶች የተውጣጡ ለኤልጂቢቲኪው+ ሰብዓዊ መብቶች የሚሟገቱ ድርጅቶች ያቀፍ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን ነው።
"በዚህ ድምፅ ውጤት፣ መንግስታት ማንንም ወደኋላ ላለመተው የገቡትን ቃል በተጨባጭ ዕውን ማድረግ እንደሚችሉ አሳይተዋል። ከ [የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት]፣ የፆታዊ ተማርኮ እና ፆታ ማንነት (ሶጊ) ገለልተኛ ኤክስፐርት ጋር መስራታችንን እንቀጥላለን" ስትል ጁሊያ አክላለች።

