ድምፅ ሳያሳሙ ይፋ መውጣት

ይፋ መውጣት በኢትዮጵያ በጣም አስከፊ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል፤ ‘ለራስ/ለግል ይፋ መውጣት' ግን ጥልቅ ጥላቻ ባለው ህብረተሰብ ውስጥ ለሚኖሩ ኤልጂቢቲኪው+ ማህበረሰብ የመፅናኛ እና የትብብር አማራጭ መንገድ ይሆናል።

በቤዛ ለዓለም

ይፋ መውጣት ወይም የግል ፆታዊ ተማርኮዋን/ዝንባሌዋን ወይም የሥርዓተ-ፆታ ማንነቶን ይፋ ማድረግ ብዙውን ጊዜ አንድ አፍታ የሚከሰት ሳይሆን፣ ቀስ በቀስ በሂደት የሚደረግ የግል የህይወት ጉዞ ነው። ትክክለኛ ወይም የተሳሳተ ይፋ የመውጫ ጊዜም የለም። ይህ ለዘብ ያለ ግንዛቤ ቢኖርም፣ በምዕራቡ ዓለም አንድ ሰው ስለማንነቱ የተጣራ እይታ ሲኖረውና ራሱን ይፋ የሚያደርግበት ጊዜና ቦታ ላይ ከደረሰ፣ ቀጣዩ ተፈጥሯዊ እርምጃ ያንን እውነት በይፋ ለመላው ህብረተሰብ ማካፈል ነው የሚል ግምት አለ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለብዙዎች፣ ኤልጂቢቲኪው+ ነኝ ብሎ ራስን ይፋ ማውጣት፤ ራስን የመግለፅ ተግዳሮት ብቻ ሳይሆን፣ በትክክለኛ ማንነት እና በደህንነት መካከል ያለውን ወሳኝ ሽግግር በጥንቃቄ ማስላትንም ይጨምራል። ፋሪስ ኩቺ ገዛኸኝ ከሁለት ዓመት በፊት ስለጉዳዩ ሲጠየቁ "አብዛኛውን ጊዜ ለእኛ ይፋ መውጣት ምርጫ አይደለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ንግግራቸው ዛሬም በማህበረሰቡ ዘንድ ይስተጋባል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የቤተ ጉራማይሌ አድቮካሲ ቡድን ተባባሪ መስራች የሆኑት ፋሪስ፣ ይፋ የመውጣት ጉዟቸውን የጀመሩት፣ በአደባባይ ከማወጃቸው ብዙ ጊዜያት በፊት ነበር። በመጀመሪያ የተመሳሳይ ፆታ ወንድ አፍቃሪ፣ ከዚያም ፌም ነን ባይነሪ (ሴት ገፅታ ተላባሽ ከሁለትዮሽ ስርዓተ ፆታ ውጪ) ግለሰብ፣ በኋላም ኩዊር ነበር።

ፋሪስ በጥቅምት ወር ብሔራዊ ይፋ መውጣት ቀንንአስመልክቶ ቤተ ጉራማይሌ ባዘጋጀው የቲክቶክ ቀጥታ ውይይት ላይ “ይፋ መውጣት ከምንም በላይ ዋናው፣ ለራስ/ለግል ይፋ መውጣት ነው” ሲሉ ገልፀዋል። ለሳቸው ይፋ መውጣት የአንድ አፍታ ክስተት ሳይሆን፣ አንድ ግለሰብ ራሱን በራስ የማስተዳደር እና ቀስ በቀስ ለማንነቱ ቋንቋ የሚሰጥበት ቀጣይ ሂደት ነው።

ፋሪስ ይህ አይነቱን ድርጊት ‘ለራስ/ለግል ይፋ መውጣት’ በማለት ይገልፁታል። በዋናነት ወደ ራስ/ግል የማየት ሂደት ሆኖ፣ ታማኝነታቸውን ያረጋገጡ የተመረጡ ግለሰቦችን ብቻ የሚጋብዝ ነው።

ይፋ የመውጣት አደጋዎችን ማመዛዘን
በሳይኮሎጂስት ሮበርት አይክበርግ እና በተመሳሳይ ፆታ ሴት አፍቃሪ አክቲቪስቷ ጂን ኦሊሪ የተመሰረተው ብሄራዊ ይፋ መውጣት ቀን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው እ.ኤ.አ ጥቅምት 11 ቀን 1988 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነበር። ከተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ነፃነት እና የሴት መብት ተሟጋች ንቅናቄዎች የተወለደው ይህ ቀን፣ በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ዙሪያ ያለውን ዝምታ ለመስበር እና የፀረ-ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ እንቅስቃሴዎችና ጭፍን ጥላቻ እይታ ውስጥ ባለመሆንና እና ችላ ማለት በተንሰራፋበት አካባቢ እንደሚሰፈን ማሳያ ለማድረግ ዓልሞ ነበር። ከጊዚያት በኋላም ዓመታዊ ቀኑ በሌሎች አገሮች ሊከበር ችለዋል።

ለአንዳንዶች፣ ብሔራዊ ይፋ የመውጣት ቀን ታይታን፣ ድፍረትን እና የራስን እውቅናን ለማክበር እድል ይሰጣል፤ ለሌሎች ደግሞ ይፋ መውጣትን በጣም አስቸጋሪ የሚያደርጉትን መሰናክሎች የሚያሳስብ ቀን ነው። 

ኤልጂቢቲኪው+ ሰዎች በወንጀል በሚከሰሱባቸው ወይም በጣም በተገለሉባቸው አገሮች “ይፋ ውጡ” የሚለው ጥሪ የማይበጅ ጥያቄ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ይህ በእውነት እና በደህንነት መካከል ያለው አሳዛኝ ምርጫ እንኳን ለሁሉም ሰው አልታደለም። ብዙዎች ካለፍቃዳቸው በአሉባልታ፣ በማጭበርበር፣ እያስፈራሩ በማስገደድ እና በኦንላይን ጥቃቶች በግዳጅ ይፋ ተደርጋዋል። ቤተሰቦች ሲራቋቸው፣ የማህበረስብ ክፍሎች ሲያባርሯቸው እና አሰሪዎች መተዳደሪያቸውን ሲነጥቋቸውም ተስተውሏል።

በኢትዮጵያ፣ በባለሥልጣናት 'ከባድ' ተብለው በሚወሰኑ የተመሳሳይ ፆታ ፆታዊ ድርጊቶች እስከ 15 ዓመት በእስራት ያስቀጣሉ። በፆታዊ ተማርኮ ወይም በሥርዓተ-ፆታ ማንነት ላይ የተመሰረተ መድልዎ ምንም አይነት የህግ ከለላ የለውም። ኤልጂቢቲኪው+ ማንነት የሚያወገዝ ብቻ ሳይሆን፤ ይህን በንቃት የሚያከናውኑት ላይም ጥላቻና ንቀትንም ያበረታታል። 

ከትምህርት ቤት እስከ የእምነት ተቋማት፣ ከፖለቲከኞች እስከ ወዳጅ ዘመዶች ድረስ መልዕክቱ ግልፅ ነው፤ ኤልጂቢቲኪው+ መሆን አሳፋሪ፣ ኃጢአተኛ፣ ባዕድ፣ የማይነገር ወይም የማይታሰብ ነው። መዘዙ ደግሞ፣ በጥላቻ የተሞላ ትንኮሳ እና ብዙውን ጊዜ ቫይራል በሚሆኑና ወደ ገሃዱ ዓለም ብጥብጥን የሚጋብዙ ማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች ነው። ፋጤ መፅሄትን ጨምሮ፣ የመብት ተሟጋቾች እና ጋዜጠኞች እነዚህን ጥቃቶችን በየጊዜው ዘግበዋል።.

ይህ አስፈሪ ሁናቴ ብዙዎች ድርብ ህይወት እንዲመሩ አስገድዷቸዋል፤ እራስን ከአደጋ ለመጠበቅ አንድ ህዝባዊ ማንነት እና የግል ማንነትን የሚያረጋገጥ ደግሞ ሌላ ማንነት። በውጭ ላሉ ኤልጂቢቲኪው+ ኢትዮጵያውያንም ይፋ መውጣት ውስብስብ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ይፋ መውጣትን፣ አገር ቤት ያሉትን ቤተሰቦቻቸውን/ጉዋደኞቻቸውን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ብለው ይፈራሉ። ሌሎች ደግሞ በማህበረሰቡ ዘንድ ያሉ የታፈኑ ድምፆችን ለማጉላት ይጠቀሙበታል። ይፋ ለሚወጡት፤ አንዳንድ ጊዜ እንደ ሁለት አፍ ሰይፍ፣ በአንድ ጎን እንደ ልዩ መብት በሌላው ደግሞ እንደ ሸክም ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል።

'ለራስ/ለግል ይፋ መውጣት' የሚያስገኛቸው ጥቅሞችን እውቅና መስጠት

ከዚህ ፈታኝ ዳራ ባሻገር ነው፣ የፋሪስ ‘ለግል/ለራስ ይፋ መውጣት’ ፅንሰ-ሀሳብ በቤተ ጉራማይሌ የቅርብ የቲኪቶክ ቀጥታ ስርጭት ላይ ከታደሙ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊዎቻቸውን ያስማማው። በግልፅ መታየት አደጋ በጣም ከፍተኛ በሆነባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ፣ ኤልጂቢቲኪው+ ሰዎች ማንነታቸውን ይፋ እንዲያደርጉ መጠበቅ ብዙ ጊዜ ህልም አንደመጨበት ነው። ራስን የመቀበል ውስጣዊ ጉዞ ላይ ማተኮር ግን፣ ግለሰቦች ይፋ መውጣትን አዳጋች ከሚያረጉባቸው ባህላዊ፣ ቤተሰባዊ እና ህጋዊ እውነታዎች እያሉም፣ ማንነታቸውን እንዲቀበሉና እንዲያከብሩ እድል ይከፍታል።

'ለራስ/ለግል ይፋ የመውጣት' ሂደት የመጀመሪያው እርምጃ፣ ይህንን የማንነትዎን ገፅታ እውቅና መስጠት እና በድፍረት፣ በእምነት እና ርህራሄ በተሞላው መንገድ ለግሎ ማወጅ ነው። ፍጹም የመሰማት አደጋ አለመኖሩን አረጋግጠው በግሎ ጮክ ብሎ መናገር/መጥራት፣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ተማርኮዎን ወይም ሥርዓተ-ፆታ ማንነትዎን ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲጎናፀፉ ሊረዳዎት ይችላል። የዚህ ሂደት እምርታዎች ለሁሉም ሰው ይለያያሉ፤ ለብዙዎች የበለጠ በራስ መተማመን እና በራሳቸው ላይ ያላቸውን ግምት የሚያሳድግ እንዲሁም ሰላማዊ ውስጣዊ ስሜትን ሊጨምር ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ውጤቶች ቀስ በቀስ በሂደት የሚመጡ ናቸው። 

አንዳንዶች መፅናኛ ካገኙ በኋላ አጋርነትን ይፈልጋሉ። ቀጣዩ እርምጃ፤ ጥንቃቄ እና ትዕግስትን የሚጠይቅ፣ ፅኑ ኤልጂቢቲኪው+ ኢትዮጵያውያን ወደ ገነቧቸውና ብዙ ጊዜ ወደማይታዩት ጠንካራ መረቦች (ኔትዎርክስ) መዞር ነው። እነዚህ የተመረጡ ቤተሰቦች በመተማመን፣ በፍቅር እና ሆንተብለው በተመሰረቱ ጓደኝነቶች በመተሳሰር፣ ዋነኛ የድጋፍ ምንጭ ይሆናሉ። እዚህ ላይ ነው ‘ለራስ/ለግል ይፋ መውጣት’፣ ሰዎች እርስ በርሳቸው የሚተማመኑበት፣ አንዳቸው ስለሌላው ማንነት ዕውቅና የሚሰጡበት፣ ክብራቸውን የሚያረጋግጡበት እና በመገለል ምክንያት የተጎዱትን ቁስሎች የሚፈውሱበት ማህበራዊ እውነታ የሚሆነው።

እነዚህ መረቦች ብዙ መልክ አላቸው። ከተዘጉ መጋረጃዎች ጀርባ በጋራ ምግብ መቋደስ፣ የቴሌግራም ቡድኖች/ቤቶች፣ በአስተማማኝ ክፍሎች ውስጥ በሹክሹክታ ሃሴት ማድረግ እና የቤተሰብ ድጋፍ ሲቋረጥ በፍጥነት የእርዳራታ እጆችን መዘርጋት ሊሆኑ ይችላል። ድምፅ አልባ ትብብር ወሳኝ የጥንካሬ ምንጭ ይሆናል። በሠላሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ ተመሳሳይ ፆታ ወንድ አፍቃሪ ኢትዮጵያዊ፣ ባለፈው ዓመት በማኅበረሰብ ትውውቅ ዝግጅት ላይ “እንዲህ ነው በሂውት መቆየት የቻልነው” ብሏል። "እርስ በርሳችን እንንከባከባለን፣ አብረን እናከብራለን፣ አብረን እንዝናናለን።"

ይፋ መውጣት በፍፁም ግዳጅ መሆን የለበትም። ዝምታም እንደ ውርደት ምልክት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ደህንነት ጥያቄ ባልሆነባቸው አካባቢዎችም ቢሆንም የግል ማንነትን መወሰን፣ ማንነትን መቼ እና እንዴት የመግለፅ ሂደት፣ ራስን በራስ የመወሰን እና የግል ተግባር ነው።

ይፋ መውጣትን አለመምረጥ ተስፋን ቆርጠናል ማለት አይደለም። ብዙ ጊዜ የህብረተሰብ ለውጥ የሚጀምረው በዝግታ ነው። ሰልፎች እና ጩኅቶች ራሳቸው የለውጥ ጅምር የሚሆኑት ከስንት አንዴ ሊሆን ይችላል። ለውጥ የሚጀምረው በትናንሽ፣ ሆን ተበልው በታቀዱና ቀጣይነት ባላቸው ግንኙነቶችና የእንክብካቤ ተግባራት ነው። በኢትዮጵያ ያለው የኤልጂቢቲኪው+ ህይወት የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰንው፣ በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅንጅትና ትብብር እና እርስ በርስ ለመደጋገፍ በሚደረገው ጥረት ከጎናቸው ለመቆም በተዘጋጁ አጋሮች ላይ ነው። አብሮነት፣ ለራሳችን እውነተኛ የመሆን ድፍረትን እና የህብረተሰቡን ውግዘት ወደ ውስጥችን ላለማስገባት የሚያግዝ ጥንካሬን ያዳብራል።

ተስፋ ማደረግ በራሱ በፅናት የምንቋቋምበት አንዱ መንገድ ነው። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ይፋ መውጣት ቀንን በግልፅ የምታከብርበት እድል ሩቅ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን የማይታሰብ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ አይነተኛ የለውጥ ተስፋ የሚደገፈውና የሚፀናው፣ ምክኒያታዊ በሆኑ ዕለታዊ እድገቶች ወይም ለውጦች ተስፋ ነው። 

ውሳኔዎ ለዓለም ወይም ለራስ/ለግል ይፋ መውጣት ይኁን፣ ለግል ደህንነቶ ሲሉ ዝምታን መምረጥ፣ ውሳኔዎ ትክክል፣ እርሶም ዋጋ ያልዎት እና ይህ ተገቢ ቦታዎ እንደሆነ ይገንዘቡ።

Scroll to Top