ፋጤ፣ በኢትዮጵያ የስራ ቋንቋ በሆነው አማርኛ እና በእንጊልዘኛ የተዘጋጀ፤ በዓይነቱ የመጀመርያ የሆነ የኤልጂቢቲኪው+ መፅሄት ነው። የእንግሊዘኛው ምህፃረቅል ኤልጂቢቲኪው+፤ በውስጡ ጌይስ (ተመሳሳይ ወንድ ፃታ አፍቃሪዎች)፣ ሌዝቢያንስ (ተመሳሳይ ሴት ፃታ አፍቃሪዎች)፣ ባይሴክሽዋል (ለወንድም ለሴትም የፆታ ተማርኮ ያላቸውን)፣ ትራንስጀንደር (የፆታ ማንነታቸወን የቀየሩትን/በመቀይር ላይ ያሉትን ሰዎች) እና ኩዊር (የፆታ ተማርኮ፣ ወሲባዊ ዝንባሌ እና ልዩ ልዩ ማንነቶች ሰብሰብ አድርጎ የሚገልፅ መጠሪያ) ሲያካትት፤ የ"+" ምልክት ደግሞ በምህፃረ ቃል ውስጥ በግልፅ ያልተዘረዘሩ ሌሎች ፆታዊ ተማርኮውችን እና የሥርዓተ-ፆታ መለያዎችን ማካተቱን ያመለክታል።

ፋጤ
ስም ወይም ቅጽል፣ አማርኛ

1. በንግግር ጊዜ የምንጠቅመው ድፍረትን፣ ማራኪ፣ አስደሳች እና አንፀባራቂ ህይወት የተላበሰን ሰው የሚገልጽ የቃል
2. በአንዳንድ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን፤ አንድ ሰው እንዚህ ባህሪያት እንዳሉት ፈታ ባለመልኩ ለማመልከት የሚጠቀሙበት፤ አንዳንዴም የፆታ ዝንባሌው ወይም የፆታ ማንነቱ የሚታይ መሆኑን ለማመልከት እንደ ኮድ ሆኖ ያገለግላል።
3. ይህንን ባህሪ ሙሉ በሙሉ በመላበስ፣ የኢትዮጵያን/የሐበሻ ኤል ጂ ቢ ቲ ኪው+ ማህበረሰብን ለማገልገል በ2017 ዓ.ም የተመሰረተ መፅሔት

- "ዋው! በባለፈው ሳምንት ዝግጅት ላይ ብዙ ፋጤህን/ሽን እያሳዩ ነበር!"
- "ሰላም ነው? አረ ፋጤህን/ሽን ቀንስ/ቀንሺ!፣ ቦታው አደገኛ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከእይታ ተደብቀው የሚኖሩትን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያን እና በመላው ዓለም የሚኖሩ የሀበሻ ዲያስፖራ ኤልጂቢቲኪው+ ሰዎች ህይወትን እና የሚመለከቷቸውን ጉዳዮች በመሸፈን ህይወት ለመዝራት እንጥራለን። ለአንባቢያን፣ ከቁም ነገር አዘል ዜናዎች እስከ ትኩስ ዘገባዎች በማድርስ፣ በዋናው የኢትዮጵያ ሚዲያ የማይታሰበውን፣ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ በሚያንፀባርቅ እና እውነተኛ በሆነ መልኩ ተወክለው እንዲያዩ እድል እንሰጣቸዋለን። ለፀሐፊዎች ደግሞ፣ በቅርበት በሚያውቁት ነገር ግን ብዙ ጊዜያት የማንነታቸውን ጉልህ ገፅታ በሚያደበዝዝው ቋንቋ በነጻነት እና ያለ አንዳች ይቅርታ ሃሳባቸውን የሚገልጹበት መንገድ አቅርበናል። ይህን ልዩ ማህበረሰብ የገነቡት ሰዎች የራሳቸው ታሪክ ደራሲና ዋና ገፀ-ባህሪያት መሆን ይገባቸዋል - እናም አሁን መሆን ይችላሉ።

የፋጤ ተልእኮ፣ ዝም ለማስባል ያለማሰለስ ጥረት እየተደረገበትም ቢሆን፣ ድምፁን ቀስ በቀስ ለማግኘት እየጣረ ያለውን ማህበረሰብ ማሳወቅ፣ ማነሳሳት እና ማበረታታት ነው። ታሪካዊ ዘገባዎች እና ጋዜጠኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘዴዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ እናምናለን። የኤል ጂ ቢ ቲ ኪው+ ኢትዮጵያውያንና ሀበሻ ዲያስፖራዎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር እና ማስጠበቅ እሳቤ በማድረግ ግንዛቤን እናሳድጋለን፣ ደንቦችንና ወጎችን እንፈትሻለን፣ እይታን እናሳድጋለን፣ ተቀባይነትን እናጎለብታለን፣ ውይይትን እናነሳሳለን፣ አጋሮችን ለመሳብ እና አንድነትን ለማጎልበት እንጥራለን። የእኛ ትኩረት ለዚህ ልዩ ማህበረሰብ ነው። ነገር ግን፣ ስለ ማህበረሰቡ እና በማህበረሰቡ ዙርያ በሚዘገቡ ታሪኮች፣ በአፍሪካ ቀንድ ክልል ውስጥ የሚገኙት ብዙሃን ተመልካቾችን አእምሮ ለመክፈት እና ልብ ለማሸነፍ እንደሚረዳም ተስፋ እናደርጋለን። በዚህ ክልል ያለውን የተቃውሞ መጠን ግምት ውስጥ እያስገባን፣ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ፋጤን፣ በመካከላቸው ለሚኖረው ለዚህ ንቁና ደማቅ የኤልጂቢቲኪው+ ማህበረሰብ የመተዋወቂያ መንገድ አድርገው እንዲመለከቱት ተስፋችን ነው። ይህም የተዳፈነውን ማህበረሰብ በማንቀሳቀስ በውስጡ የታቀፉትን ግለሰቦች ሰብአዊነት ማጎናፀፍ ነው።

ውሎ አድሮ ወደ መፅሄታችን እግር ጥሎአቸው የሚመጡትን አንባቢዎች፣ በፆታዊ ተማርኮውችን እና የሥርዓተ-ፆታ መለያዎቻቸው ምክንያት፣ ሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጎጂ መላምቶችን ለመከላከል በድፍረት፣ እንደ ግብዓት እንዲጠቀሙበት እና ሌሎችም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ለማህበረሰቡ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት የሚያነሳሳ እንደሚሆንም ተስፋችን ነው። ይህም ደህንነትን፣ መከባበርን እና እኩልነትን ለማስፈን የመጀመሪያው እርምጃ፣ አልፎም ሁሉን አቀፍ ህብረተሰብ ለመፍጠር የምናደርገውን ተመሳሳይ፣ ረጅም እና ጠመዝማዛ መንገድ እንደሚሆንም እናምናለን።

ፋጤ ለማነቃቃት ብቻ ሳይሆን ለማስተማርም ይጥራል። የኢትዮጵያውያንን/የሐበሻ ኤልጂቢቲኪው+ ማህበረሰብ እየደረሰበት ያለውን ትግል፣ አደጋ፣ ስደት እና ወንጀለኘነት ሳንደባብስ፣ የተስፋ፣ የፍቅር፣ የጽናት እና የድል ታሪኮችን እናካፍላለን። ለአስተዋጽዖ አበርካቾቻችን እና ለባለጉዳዮች ደህንነት ቅድሚያ መስጠት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ የደበዘዙ ምስሎችን እና ተለዋጭ ስሞችን ለብዙ ጊዜያት በይዘታችን ውስጥ እንደሚታይ ልናሳውቃችሁ እንወዳለን። ግባችን በህብረተሰቡ ውስጥ በጣም አስፈላጊ ለውጦችን ማቀጣጠል ነው። እስከዚያው ድረስ ግን የማህበረሰቡን አባላት ትኩረት ወደ ጤናማ ይዘት መሳብ መቻል ወይም በቀላሉ አንድ ተስፋው የመለመለን ሰው እንዲፀና ማነሳሳት የፋጤ የስኬት ማሳያ ይሆናል። የፋጤ አንድምታ አዝናኝ አንዳንዴም አስቂኝ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ያለ አንዳች ግልፅነት አንባቢዎቻችንን ማነቃቃት ይቻላል ብለን አናምንም። ለዚህም፣ የኢትዮጵያውያንን/የሐበሻ ኤልጂቢቲኪው+ ሰፊና እና ውስብስብ ጉዞ እንዲሁም አንዳንድ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃርያን ማንነታቸውን ለማመልከት የሚጠቀሙበትን እና ከአማርኛ የተወረሰውን ‘ዜጋ’ የሚለውን ማንነት ጨምረን በመዳሰስ፣ በዚህ እያበበ ባለው ማህበረሰብ ውስጥ፣ ከመደበኛው አንስቶ ወጣ እስካለው እንዲሁም በመካከሉ ያለውን ሁለንተናዊ የህይወት ተሞክሮዎች በማሳየት ይህንን እውን እናደርጋለን።

ፋጤ ትልቅ ምኞቶችን አንግቧል። ማህበረሰቡን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል እና ከአጎራባች ማህበረሰቦች ጋር ያለውን ግንኙንት እንዲጠናከር ለማገዝ፣ የመጽሔቱን እትሞች እና ትርጉሞች በሌሎች የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቋንቋዎች እንደምንለቅ ተስፋ እናደርጋለን። በአህጉሪቱ ውስጥ ያሉ የኤልጂቢቲኪው+ እንቅስቃሴዎችን መከታተል አስፈላጊ መረጃን ያቀርባል። ይህም የጋራ ተግዳሮቶችን፣ ጠቃሚ የመማር እና የትብብር እድሎችን ይከፍታል። በተጨማሪም ድንበር ተሻግረው፣ በአንድ ዓላማ ተሳስረው፣ ለፍትህ የሚታገሉ ማህበረሰቦችን፤ በስኬቶቻቸውም ሆነ እንቅፋት በሚያጋጥማችው ጊዜ የአብሮነት ስሜትን ያሳድጋል። እራሳችንን ክልላዊ ማዕከል አድርግን ለመመስረት የበለጠ ለመስራት ዓላም አድርገን፣ ፓን አፍሪካዊ ዜናዎችን የምንዘግበውም ለዚህ ነው።

በርካታ ገፅታ፣ ስብዕና እና የተለያዩ አመለካከቶች ያላቸው፣ ኤልጂቢቲኪው+ ሰዎችን በሀገር፣ በአህጉር አልፎም ከመላው ዓለም ካሉ ሰዎች ጋር እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ መርዳት፤ ቀጣዩ ዓላማችን ነው። እነዚህን አንዳንድ ጊዜ የተበታተኑ ማህበረሰብ ክፍሎች አንድ ለማድረግ፣ ልዩ የሆነውንና የሚያስተሳስራቸውን ባህሎቻቸውን ትርጉም ባለው መንገድ ለማሳደግ እና ለመርዳት፣ ከአለምአቀፉ የኤልጂቢቲኪው+ ማህበረሰብ ጋር እንተባበራለን።

ደፋር ለውጥ ፈጣሪዎች እንሁን! አሳቢ እና ገንቢ መሆን አንዘንጋ። ብልህ፣ ቅን እና ከምንም በላይ ሃሳብ የማመንጨት ችሎታን በመጠቀም አሳማኝ እንሁን። ለዚህ አስፈላጊ ጉዳይ የመናገር ኃይልን እንጠቀም።

ፋጤን ተቀላቀሉ።

Scroll to Top